የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የከተማዋን የጤናው ዘርፍ አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ ሆስፒታሎች ጋር በዛሬው እለት ወረዳን መሰረት ያደረገ ዕቅድ ማቀድ ጀምረዋል ። በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በ2018 በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደር የተሻለ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። የጤና አገልግሎቱን ውጤታማ ለማድረግ ከዕቅድ ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ያሉት ዶክተር ዮሐንስ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ውጤታማ የጤናው ዘርፍ ተግባራት የሚከናወኑበት እንደሚሆንም ተናግረዋል። ሆስፒታሎች ከተማዋ ከሃገርም ባለፈ እንደ አህጉር ውጤት ያስመዘገበችበትን እና ብቁ ሀገር ተረካቢ ተውልድ ለማፍራት በትኩረት እየሰራችበት ያለውን የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን በዕቅዱ በማካተት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ዶክተር ዮሐንስ አሳስበዋል። የዕቅድ መርሐ-ግብሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ ተገኝተው ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል።